ለቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ መጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ተሰጠ፡፡
Posted by admin on Friday, 17 January 2025

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ታህሳስ 08/2017
ሥልጠናዉ የተዘጋጀው በዩኒቨርሲቲዉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈፃሚ አስተባባርነት ሲሆን ሥልጠናው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በዩኒቨርሲቲዉ ካሉት የተለያዩ ትምህርት ክፍሎች በተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡
በሥልጠናዉ ላይ ተገኝተዉ ተገቢውን መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲዉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ተስፋነሽ ኢዴኤ ሲሆኑ የሥልጠናዉ ዓለማ ወደ ዩኒቨርሲቲዉ እየገቡ ያሉ ተማሪዎች በዕዉቀትና በክህሎት ላይ የተመሠረቱ ዉሳኔዎችን የመወሰን ብቃት በማዳበር በህይወታቸዉ ዉስጥ የሚገጥማቸዉን ፈተናዎች ወደ መልካም አጋጣሚዎች በመቀየር ለዉጤት እንዲበቁ ታስቦ የተዘጋጀ ሥልጠና ስለመሆኑ አስረድቷል፡፡
አያይዘዉም ወ/ሪት ተስፋነሽ ኢዴኤ ሲገልጹ; ተማሪዎች ከምንም በላይ የመጡበትን ዓላማ በማወቅ ለአላማዉ መሳካት እንዲሠሩ፤ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት ከተማሪዉ ጎን የዩኒቨርሲቲዉ ማህብረሰብ እገዛ የሚያደርግ ስለመሆኑ ጭምር አንስተው በግቢዉ ቆይታ ወቅትም ከዉጪም ሆነ ከዉስጥ የሚገጥሙ ችግሮችን በመለየት ሳይዘገይ መፍትሄ እየሰጡ መሄዱ አስፈላጊ መሆኑንም አንስቷል፡፡
ሥራ አስፈፃሚዋ በመጨረሻ ባስተላለፉት መልዕክት ለተማሪዎች የሚደረገዉ ድጋፊ በአንድ ጊዜ በሚሰጥ ሥልጠና ላይ ብቻ የሚያበቃ አለመሆኑንና ቀጣይነት ባለው መልኩ በዋናነት፤ሴት እህቶችን ከፆታዊ ጥቃት ራሳቸዉን እንዲከላከሉ፤ከኤቺ አይቪና መሰል በሽታዎች ራሳቸዉን እንዲጠብቁ፤በመማር ማስተማሩ ሂደት እርስ በርስ እንዲደጋገፉና በተለይም አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን በተሳሳቱ አመለካከቶች ከትምህርታቸዉ እንዳይስተጓጉሉ ትኩረት ተሰጥቶ የመደገፍ ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑ ገልፀዋል፡፡
በሥልጠናዉ ላይ የብዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መ/ር የሆኑት ዶ/ር ዳዊት ኡደሳ ተማሪዎች ለነገ የተሻለ ሕይወት እንዴት መድረስ ይቻላል የሚለዉን ዓለማ በማንገብ ፤የጊዜ አጠቃቀምን በማሻሻል፤ቅድሚያ የሚሰጡ ጉዳዮችን በመለየትና ዉጤታማ የአጠናን ዘዴን በመከተል እንዲሁም በጓደኛ የሚመጣ አላስፈላጊ የአቻ ግፊትን /peer pressure/በመቋቋምና በራስ የመተማመን መንፈስን በማዳበር ስኬታማ ሆኖ ማጠናቀቅ እንደሚቻል የሕይወት ተሞክሯቸዉን ጭምር አካፍሏል፡፡
በተጨማሪም ሥልጠናዉ የሶሻል ሳይንስ መ/ርት በሆኑት በመ/ርት አረጋሽ ኢቲቻ አማካኝነት ተማሪዎች በህይወት ልምዳቸዉ ራስን በማወቅና ራስን በመሆን፤በራስ መተማመን በማጎልበት፤የሌሎችን ተጽዕኖ በመቋቋም፤አካዳሚክ ክህሎትን በማዳበር፤ግቦችን በማስቀመጥና ዉጤታማ አጠናን ዘዴን ተጠቅሞ ለዉጤት መብቃት ይቻላል በሚሉት ዙሪያ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን መ/ርት እየሩሳለም መንግስቱም ከህግ ትምህርት ቤት ፃታዊ ጥቃትን አስመልክቶ ለፆታዊ ጥቃት የሚዳርጉ ጉዳዮች፤ፆታዊ ጥቃት ከደረሰ በኃላ የሚወሰዱ መፍተሄዎችና በመሳሰሉት ዙሪያ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን መ/ርት ቃልኪዳን በጅቷል ከጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስለ አቻ ግፊትና ምንነት አስመልክተው ሥልጠናዉን ከሰጡት መካከል ይገኛሉ፡፡