በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የምርምር ሥራዎች ዙሪያ የዉስጥ ግምገማ ተካሄደ፡፡

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ፣ መስከረም፣ 2018 (ቡሆዩ)

በዩኒቨርሲቲዉ የምርምር፤ስርፀትና ሥነ ምግባር ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት ከተለያዩ ኮሌጆች የተወጣጡ ምሁራን የምርምር ሥራዎቻቸዉን አቅርበዉ የዉስጥ ግምገማ ተካሂዶባቸዋል፡፡

በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ምርምር፤ስርፀትና ሥነ ምግባር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አብነት በቀለ ሲሆኑ ለዉስጥ ግምገማ የቀረቡ የምርምር ሥራዎች በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ዳይሬክቶሬቱ ጭብጥ ተኮር የምርምር ሥራዎችን ለማሰራት ያስቀመጠዉን አቅጣጫ ተከትሎ በተለያዩ ኮሌጆች ምሁራን ፕሮፖዛል ቀርበዉ፤ተገምግመዉና ተቀባይነት አገኝተዉ የተሠሩ የምርምር ሥራዎች ስለመሆናቸዉ በመግለጽ በጋራ የዉስጥ ግምገማ መደረጉ የእርስ በርስ ልምድ ልዉዉጥ እንዲደረግ ታሳቢ በማድረግ እንደ ሆነ ገልፀዋል፡፡

አያይዘዉም ዶ/ር አብነት የዉስጥ ግምገማ የተካሄደባቸዉ የምርምር ሥራዎች በዳይሬክቶሬቱ በኩል በተደረገ ገንዘብ ድጋፍ የተሠሩ 39 የምርምር ሥራዎች መሆናቸዉን በማስታወስ በሀገር ደረጃ ለፖሊስ ግብዓት የሚሆኑና ወደ ተግባር ተቀይረዉ በአካባቢዉ የሚታዩ ችግሮችን ሊፈቱ የሚችሉ የምርምር ሥራዎች መሆናቸዉን ገልጸዋል፡፡