በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የፀረ-ጾታ ጥቃት፤የፀረ-ኤድስ እና የአካል ጉዳተኞች ቀን ተከበረ፡፡

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ታህሳስ 12/2017 ዓ.ም (BHU)
በዚህ አመት የፀረ-ፆታ ጥቃት በአለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ ‹‹የሴቷ ጥቅት የእኔም ነዉ ዝም አልልም! ›› በሚል መሪ ቃል፤ በሌላ በኩል የፀረ-ኤድስ ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ37ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ36ኛ ጊዜ ‹‹ሰብዓዊ መብት ያከበረ ኤች አይ ቭ አገልግሎት ለሁሉም!›› እንዱሁም የአካል ጉዳተኞች ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ32ኛ ጊዜ ‹‹የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ!››በሚል መሪ ቃል የዩኒቨርሲቲዉ የሥራ ኃላፊዎች ፤ሰራተኞችና ተማሪዎች በተገኙበት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ታጅቦ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ምርምር፤ስርፀትና ሥነ ምግባር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አብነት በቀለ ሲሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ከሌሎች በተሻለ መልኩ የተለያዩ ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጣሱ የሚጠበቁበት አካባቢ ቢሆንም አሁንም መሻሻል ያለባቸዉ እንደ ፆታዊ ጥቃት ዓይነቱ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየታዩ መሆናቸዉን በመጥቀስ ይህን መቅረፍ የሚቻለዉ በትምህርትና በእንደዚህ ዓይነት የሥርዓተ ጾታ በኩል በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ በመገኘት የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨባጫ ሥራዎችን በመሥራት መሆኑን አስረድቷል፡፡
በተጨማሪም በበዓሉ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲዉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ተስፋነሽ ኢዴኤ ፆታዊ ጥቃትን በሚመለከት የነገ ሀገር ተረካቢ ታዳጊ ሴቶች ላይ የሚደርሰዉን ፆታዊ ጥቃት ለመቀነስ ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን በመጥቀስ ይህንኑ በመቀነስ ረገድም የወንዶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ሴት እህቶቻችንን ከጥቃት ለመከላከል ተረባርበን መሥራት አለብን ብሏል፡፡
ሥራ አስፈፃሚዋ አክለዉም የፀረ-ኤድስ ቀን በሚመለከትም በአሁኑ ሰዓት በሽታዉን አስመልክተው የሚደረጉ ቅስቀሳዎች አናሳ በመሆናቸዉ ሰዎች ለበሽታዉ ብዙም እየተጠነቀቁ እንዳልሆነና ነገር ግን በሽታዉ እንደገና በማስፋፋት ላይ ያለ ስለመሆኑ ጠቅሰዉ የነገ ሀገር ተረካቢና አምራች ዜጋ ለመሆን ራስን ከበሽታዉ መከላከል አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ወ/ሪት ተስፋነሽ ኢዴኤ የአካል ጉዳተኞችን ቀን በሚመለከት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን አካል ጉዳተኝነት ከየትኛዉ ሥራ የማያግድ መሆኑን በመጥቀስ ነገር ግን በማህብረሰባችን በኩል በተሳሳቱ አመለካከቶች ወደ ኃላ እየቀሩ እንደሆነና ይህንን ለመቅረፍም አስተሳሰባቸዉን በመቀየርና አካል ጉዳተኞችን በመደገፍ አጋርነታችን መግለጽ አለብን ብሏል፡፡
በዕለቱም የህግ ት/ቤት መ/ርት በሆኑት መ/ርት ኃያልነሽ ግርማ እና መ/ርት ቃልኪዳን በጅቷል አማካኝነት ፆታዊ ጥቃትንና የኤች ኣይቨ በሽታን አስመልክተው አጠር ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡