ተመራቂዎች የቀሰሙትን እውቀት የሕብረተሰቡን ችግሮች በሚፈቱ የምርምር ስራዎች ላይ ሊያውሉት ይገባል

ቡሌ ሆራ፤ሰኔ 14/2017 (ኢዜአ)፡-ምሩቃን የቀሰሙትን እውቀት የሕብረተሰቡን ችግሮች በሚፈቱ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊያውሉት እንደሚገባ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ደጀኔ አየለ ገለጹ።
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ለ14ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1ሺህ 232 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
ከተመራቂዎች መካከል 13ቱ በሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ መሆኑም ተነግሯል።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ደጀኔ አየለ እንደገለጹት ፤ ተቋሙ በግብርና፣ በማዕድን፣ በሀገር በቀል እውቀትና በጤና የትኩረት መስኮችን በመለየት ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ቴክኖሎጂ የማፍለቅ ሃላፊነቱን እየተወጣ ነው።
ተመራቂዎችም በብርቱ ጥረት ያገኛችሁትን እውቀትና ክህሎት በሃላፊነት በመጠቀም ሀገርና ህዝብን ማገልገል ላይ ማዋል አለባችሁ ብለዋል።
በተለይም በአካባቢያቸው የማህበረሰብ ችግሮች ላይ በማተኮር በምርምርና ጥናት፣በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና መሰል ዘርፎች አርአያነት ያለው ተግባር ማከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል ።
ዩኒቨርሲቲው በ172 የትምህርት መስኮች ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያሰለጠነ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃኑ ለማ (ዶ/ር) ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ለ14ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 232 ተማሪዎች ማስመረቁን አንስተው፤ ከዚህም ውስጥ 13ቱ በሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ምሩቃን የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም ፈተናዎችን በመፍታት በተሰማሩበት የስራ መስክ ለውጤት እንዲበቁም አሳስበዋል።
ከተመራቂዎች መካከል በአመራርና ለውጥ አስተዳደር የሶስተኛ ዲግሪ ተመራቂ ከበደ አሰፋ በሰጠው አስተያየት፤ በቀሰመው እውቀት ሀገሩን በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
በተማረችበት የትምህርት ዘርፍ ከራሷ አልፋ ሀገሯን ለመጥቀም እንደምትጥር የገለጸችው ደግሞ በሶፍት ዌር ኢንጅነሪንግ የማዕረግ ተመራቂ ፌኔት ጌታቸው ናት።
በሀገር ደረጃ ለቴክኖሎጂው ዘርፍ እድገት የተሰጠውን ትኩረት በመጠቀም በተለይም በኮዲንግና ሰው ሰራሽ አስተውሎት እውቀቷን ለማዳበር እንደምትተጋ አመልክታለች።