የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ አደርገ::
Posted by admin on Friday, 4 February 2022
የወሎ ዩኒቨርሲቲ በጦርነቱ ምክንያት ዉድመት ከደረሰባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ነው። በትምህርት ሚኒስቴር እና ኒቨርሲቲዎች በጋራ ጥምረት የተቋማቱን ጉዳት በመለየትና መልሶ ለማቋቋም ዩኒቨርሲቲዎች በሶስት ክላስተር ስር ተዋቅረዋል፡፡ በዚሁ መሰረት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ክላስተር ስር ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ዉስጥ አንዱ ሲሆን፤ለወሎ ዩኒቨርሲቲ መልሶ ማቋቋሚያነት ያግዛሉ የተባሉ ድጋፎችን አድርጓል፡፡ በመሆኑም ግምታዊ ዋጋቸው ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የቁሳቁስ ድጋፍ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ አስረክቧል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የድጋፉ አስተባባሪ ኢንጅነር ጀማል ወርቁ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ጉዳት እኛንም ያሳስበናል በማለት በቻልነው አቅም ያለንን ለማካፈል መጥተናል ሲሉም ተናግረዋል ።
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በርካታ ውድመቶች እና ዝርፊያ የደረሰበት በመሆኑ መልሶ ለማቋቋም ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ዩኒቨርሲቲው ባጠናው ጥናት ማረጋገጡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር እና የድጋፉ አሰባሳቢ አቶ ጢሶ ጎበና በበኩላቸው በወሎ ዩኒቨርሲቲ ላይ የደረሰው ጉዳት የሚያሳዝን ቢሆንም ጉዳቱ በዩኒቨርሲቲዎች መካከል የተጠናከረ መደጋገፍ እንዲኖር አድርጓል ብለዋል።
በተጨማሪም ቡድኑ በስፍራው በመገኘት ድጋፉን ለወሎ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ካስረከቡ በኋላ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የደረሰውን ዉድመት ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት በወሎ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አወል ሰይድ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲዎች እያደረጉት ያለው ድጋፍ አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዉ፣ ዩኒቨርሲቲዎቹ ላደረጉት ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።
በቀጣይ ወር የወሎ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራውን እንደሚጀመር ዶክተር አወል ጠቁመዋል፡፡
ለላቀ ለውጥ እንተጋለን !!!
ጥር 27/2014 ዓ.ም