የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የ2016 ዓ/ም የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት የሚወስዱ የ”STEM”ተማሪዎችን መቀበል ጀመረ
ሀምሌ 27/2016 ዓ/ም
በዙሪያዉ ካሉት የተለያዩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተወጣጡ እነዚህ ተማሪዎች ከየትምህርት ቤታቸዉ በትምህርት አቀባበላቸዉ ከሌሎች የተሻሉና እንዲሁም የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸዉ ወይም ልዩ ፍላጎት /Special Gift /talency/ ያላቸዉ መሆናቸዉን ቀደም ሲል ከነበረዉ የተማሪዎች ፕሮፋይል መረዳት ተችሏል።
በ”STEM” ተማሪዎች የአቀባበል ፕሮግራም ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲዉ ከፍተኛ የስራ አመራር መካከል ዶ/ር ብርሃኑ ለማ የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት፣ዶ/ር ትንሳኤ ታምራት የአካዳሚክ የምርምር የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንትና እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኑጉሴ ጎዳና ሲሆኑ ፕሮግራሙን በማስመልከት አላማዉንና የትኩረት አቅጣጫዉን ለተማሪዎቹ በትክክል በመግለጽ ዩኒቨርሲቲዉ ይህንን ፕሮግራም ለወደፊቱም ቢሆን በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል ለተማሪዎቹ ቃል ግብተዋል።
እነዚህ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲዉ በሚኖራቸዉ ቆይታ አብዛኛዉን ግዜ የሚያተኩሩባቸዉና የሚሰጧቸዉ ትምህርቶች ሶስቱ የተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፎች (ኬሚስትሪ፣ፊዚክስና ባዮሎጂ) እንዲሁም ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብን ያማከለ ሲሆን ተማሪዎቹ በተሻለ መምህራን እንዲረዱና እንዲማሩ እድል ይፈጥራላቸዋል ተብሎ ይታመናል።
ከትምህርቱም ጎን ለጎን እንደ ኮምፒዩተር ሳይንስና መሰረታዊ የኮምፒዩተር ክህሎቶች እንዲወስዱ እንደሚደረግ ከተገኘዉ መረጃ መረዳት ተችሏል።በተጨማሪም ፕሮግራሙ ወደ ዩኒቨርሲቲዉ ከመጡት ተማሪዎች መካከል ልዩ ተሰጥኦ(Talency)ያላቸዉን በመለየት ወደፊት ያላቸዉን የተፈጥሮ ስጦታ በትክክል አዉጥተዉ እንዲያሳዩ መደላድል የሚፈጥርላቸዉ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
በዩኒቨርሲቲዉ ግቢ በሚኖራቸዉ ቆይታም በዩኒቨርሲቲዉ ባሉት የተለያዩ ፋሲሊቲዎች ማለትም ላቦራቶሪ፣ዎርክሾፕችና ሰርቶ ማሳያዎች በመጠቀም በዉስጣቸዉ ያለዉን እዉቀት፣ክህሎትና ዝንባሌ የበለጠ አጉልተዉ በማዉጣት የወደፊት የአካዳሚክ ጉዞቸዉን መንገድ እንደሚጠርግላቸዉ ከተቀመጠዉ የፕሮግራሙ አላማና ግብ መረዳት ተችሏል።