በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ማህበር ሥራ አስፈፃሚዎች ምርጫ ተካሄደ።

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ፣ ግንቦት 9፣ 2017 ዓ.ም (ቡሆዩ)
በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ በንቲ እና የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደበላሽ መንግስቱ በተገኙበት ከእያንዳንዱ ኮሌጅ ከተወከሉ መምህራን ጋር የጋራ ውይይት ተካሂዶ የማህበሩ ሥራ አስፈፃሚዎች ምርጫ ተካሂዳል።
የማህበሩ ከፍተኛ አመራሮች በዩኒቨርሲቲው የመጡበትን ዓላማ እና ማህበሩ የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያም ሆነ የመምህራንን ጥቅማጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር እያከናወነ ባለው ሥራ ዙሪያ ገለፃ አድርጓል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ በንቲ በበኩላቸው የመምህርነት ሙያ ለሙያዎች ሁሉ መሠረት መሆኑን፣በሁሉም ረገድ መምህራን ያላቸው ድርሻ በጉልህ የሚጠቀስ ስለመሆኑ እና ሁሉም ሰው በሕይወት ዘመኑ አንድ የሚያስታውሰው መምህር ያለ ስለ መሆኑ ያነሱ ሲሆን ይህን ታላቅ ሙያ በሚገባው ልክ ለማስጠራት ማህበሩ በሚገባ እንዲደራጅ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
አያይዘውም ዶ/ር ዮሐንስ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመምህራን ማህበር በተደራጀ መልኩ በአምስት መሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን፣የማህበሩን አመራሮች ምርጫን በሚመለከት ከታች ከወረዳዎች ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ የራሱ ጊዜ ሠለዳ ተቀምጦለት ፊትሃዊ በሆነ መልኩ ምርጫዎች ሲካሄዱ የቆዬ መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን ይህ በዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ ሲታይ የተጠናከረ ባለመሆኑ በየዩኒቨርሲቲዎች በመገኘት የማደራጀት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደበላሽ መንግስቱ በዩኒቨርሲቲዎች በኩል በዋናነት ትኩረት ተሰጥተው ማከናወን ከሚጠበቅባቸው ተግባራት መካከል አንዱ የመማር ማስተማር ተግባር መሆኑንና ይህ ተልዕኮ እንዲሳካም ግምባር ቀደም ተዋናይና ፈፃሚዎች መምህራን በመሆናቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደረጃ ማህበሩን በማጠናከር ለትምህርት ጥራቱ ማረጋገጥም ሆነ በመምህራን መብትና ጥቅማጥቅም መከበር ዙሪያ መስራቱ ተገቢና ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።
ከተሳታፊዎችም ከትምህርት ጥራቱ መረጋገጥ ጋርም ሆነ ከመምህራን መብትና ጥቅማጥቅም መከበር ጋር ተያይዞ ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች የማህበሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከትምህርት ሚኒስቴር ጋርም ሆነ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር በቅርበት እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች ዙሪያ፣በተሠራው ሥራም የመጣውን ለውጥና በቀጣይም እንዲስተካከሉ ጥያቄዎች ቀርበው በሂደት ላይ ባሉ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የዩኒቨርሲቲውን መምህራን ማህበር ሥራ አስፈፃሚዎች ምርጫን በሚመለከት በመመሪያውና ደንቡ ዙሪያ አጠር ያለ ማብራሪያ ከቀረበ በኃላ እያንዳንዱ ኮሌጅ የራሱን ተወካዮች እንዲመርጥ ተደርጎ ከተመረጡት መካከልም በድምፅ ብልጫ እንዲመረጡ ተደርጓል።
በተደረገው ድምፅ አሰጣጥ መሠረት መ/ር ብርሃኑ ተስፋዬ የማህበሩ ፕሬዝዳንት፣መ/ሪት ገላኔ ዲሪባ ም/ፕሬዝዳንት፣ጌታቸው ነመራ ዋና ፀሐፊ፣ኢየሩስ ካሡ ም/ዋና ፀሐፊና ሥርዓተ ፆታ ተጠሪ፣ታደሰ ጂሎ ትምህርትና ሥልጠና ተጠሪ እንዲሁም መ/ር መሠረት መርድኪዮስ ኦዲተር ሆነው የተመረጡ ሲሆን የተመረጡ የማህበሩ ሥራ አስፈፃሚዎችም ዶ/ር ዮሐንስ በንቲና ዶ/ር ደበላሽ መንግስቱ በተገኙበት ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማ ጋር ትውውቅ ተደርጎ የሥራ አቅጣጫ ተሰጥቷቸዋል።